ሰኞ 19 ኦክቶበር 2015

አሳ ነክ ወጎች (ክፍል ፪)



አሳ ነክ ወጎች (ክፍል ፪)

ባለፈው እንዳልነው የነገደ-ወይጦ አገር አባይና ጣና ናቸው፡፡ ማንነታቸው የተቀዳው እንደውሃው ከባህሮቹ ነው፡፡ ይህም የውሃ ነዋሪው ጦጣ (Aquatic Ape Theory) የሚለውን የዝግመተ-ለውጥ መላምት እንድናስታውስ አድርጎናል፡፡ ጉዟችን በቦታና በጊዜ ላይ የሚደረግ በመሆኑ የጉዞ ማስታዎሻችንም በቦታና በጊዜ ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ አሁን በጊዜ ላይ የምናደርገውን ጉዞ እንቀጥላለን፡፡ ስለጦጣው ትንሽ ላውጋችሁ፡፡

እንደወይጦዎች ከአሳ ወገን የሆነው ጦጣ በውሃ ውስጥ ይኖር ነበር፡፡ ይህ በውሃ ውስጥና ውሃ ዳር ለዳር የሚኖር የጦጣ ዝርያ የሁላችንም ቅድመ-ቅድመ-አያት ነው፡፡ የሰው ልጅ የአሁንን ቅርፅና ተፈጥሮ ያዳበረው እንደጉማሬ በውሃ ውስጥ ይኖር ስለነበር ነው፡፡ በዚህ መላ-ምት መሰረት የሰው ልጅ ገዳይ ጦጣ አልነበረም፡፡ የሴቶችም ሚና ልጅ በማሳደግ የተወሰነ አልነበረም፡፡ ከወንዱ ጋር እኩል ውሃው ውስጥ እየተዘዋወሩ የሚበላ አሳ ነክ ነገር ይሰበስቡ ነበር፡፡ ይህ ሃሳብ ለፌሚኒስቶች ጥሩ ስንቅ ይሆናችኋል፤ ተጠቀሙበት፡፡

የሌሎች እንስሳት አንጎል እየተጨማተረ ሲሄድ የሰው ልጆች አንጎል ግን እየፋፋ ከቦርጫችን የማይተናነስ የሆነበት ምክንያት በውሃ ውስጥ ብቻ የሚገኙ ንጥረ-ነገሮችን ለመመገብ ዕድል ስላገኘን ነው፡፡ ጎረቤታችን ጉማሬ ነበር፡፡ እንዲህ አሁን ሰልጥነን ውለታቸውን ብንረሳም ከነአምባዛ ጋር ክፉ ደጉን አሳልፈናል፡፡

ሌላው የውሃ ህይወታችን ምስክር አተነፋፈሳችን ነው፡፡ ሶስት ዓይነት የአተነፋፈስ መንገዶች አሉ፡፡ በፈቃድ፣ ያለፈቃድና ሁለቱንም አተነፋፈስ የሚጠቀሙ አሉ፡፡

እንግዲህ በየብስ ላይ የሚኖሩ አጥቢዎች ሁሉ የሚተነፍሱት ከራሳቸው ቁጥጥር ውጭ በሆነ ሁኔታ ነው… ያለፈቃዳቸው፡፡ ሙሉ በሙሉ በንቃተ-ህሊና ውስጥ ሆነው በራሳቸው ፍቃድና ቁጥጥር የሚተነፍሱ እንስሳት ዶልፊንና አሳ ነባሪ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ግማሽ ያንጎላቸው ክፍል ብቻ እንቅልፍ የሚተኛው፡፡ ሙሉ ለሙሉ ከተኙማ ትንፋሹን ማን ይቆጣጠርላቸዋል?! ስለዚህ መተንፈሳቸው ስለሚያቆም ሞት ይወስዳቸዋል፡፡ ይህ እንዳይሆን በግማሽ ጎናቸው ሳይሆን በግማሽ አንጎላቸው ይተኛሉ፡፡ እግዜር ያሳያችሁ እነዚህ ምስኪኖች እንዴት ያለ እንቅልፍ እንደሚተኙ፡፡ ሶስተኛው ቡድን እንደየሁኔታው በንቃተ-ህሊና ውስጥ ሆኖ በራሱ ቁጥጥር የሚተነፍስ አልያም ደግሞ ያለቁጥጥሩ እንዲሁ የሚተነፍስ የእነእንቁራሪት ወገን ነው፡፡ ይህ ወገን በየብስና በውሃ ላይ እያፈራረቀ የሚኖርና ውሃ ውስጥ ሲገባ ትንፋሹን በመቆጣጠር የሚተነፍስ ነው፡፡

የሰው ልጅ እንደእንቁራሪት ትንፋሹን በመቆጣጠር የሚኖር ከመሰሎቹ የተለዬ ብቸኛ ፍጡር ነው፡፡ ይህን ባህርይ ከዬት አመጣው ነው ጥያቄው እንግዲህ፡፡ ይህ ባህርይ ከውሃ ዳር ኗሪነቱ የመጣ ነው ይሉናል ሊቃውንቱ፡፡

ነገደ-ወይጦ ይህን የባህር ውስጥ ህይወቱን የረሳ አይመስልም፡፡ የአሳን ውለታ ሊረሳ አልፈቀደም፡፡ የጥንቱን ከተማውን መርሳት አልፈለገም፡፡ ውሃ ዳር ኑሮውን ይገፋል፤ ውሃው ውስጥ ቀለቡን ይፈልጋል፡፡…

የውሃ ዳር ጦጣ መላ-ምት እንደሚለው ከውሃ አቅራቢያ የሚኖሩ ቀደምት ነዋሪ የዓለም ህዝቦች ልጅ የሚወልዱት ወደባህር ሄደው ነው፡፡ ሚሲዮኖች መጥፎ ልማድ ነው ብለው እስኪያስተዋቸው ድረስ እናቶች ልጆቻቸውን የሚወልዱት ወንዝ ዳር ወርደው ነው፡፡ ምጥ ሲጀምራቸውም አምቡላንስ የሚጠሩት ወደ ሆስፒታል ሳይሆን ወደ ወንዝ እንዲወስዳቸው ነው፡፡ እናቶችም በአሳ ስጋ እንጅ በገንፎ አይታረሱም ነበር፡፡ ነበር ነው እንግዲህ፡፡

ህፃናቱ ታዲያ ከመራመዳቸው በፊት ዋና ይችሉ ነበር፡፡ የሰው ልጅ ዳይቪንግ ሪፍሌክስ ፊታችን ውሃ ላይ ባረፈ ጊዜ ጉረሮአችንን እንዲዘጋ ስለሚያደርግ ህፃናቱ እንደልባቸው ይዋኙ ነበር፡፡

ይህን የህፃናቱንና የባህር ግንኙነት በቅዱስ መፅሃፍ ውስጥም እናገኘዋለን፡፡ እባካችሁ ኦሪት ዘፀዓት ላይ ግለጡ፡፡… የደንገል ሳጥን ለእርሱ ወስዳ ዝፍትና ቅጥራን ለቀለቀችው፤ ህፃኑንም አኖረችበት፤ በወንዝም ዳር ባለ በቄጤማ ውስጥ አስቀመጠችው…ይላል፡፡ የደንገሉን ሳጥን ማን ሰራላት? ወይጦ፡፡ የሆነስ ሆነና ማነው ይህ ህፃን? ሙሴ፡፡ የስሙም ትርጓሜ ከውሃ አውጥቼዋለሁ ማለት ነው፡፡ በስያሜውና በሌሎች የሙሴ ማንነት ዙሪያ ማንበብ ብትሹ የሲግመንድ ፍሮይድን “Mosses and Monotheism” ግለጡ፡፡ በፍሮይድ ገለፃ ውስጥ ሙሴ ማለት የግብፅ ቃል ነው፤ ትርጓሜውም ህፃን ማለት ነው ሲል ሌላ ፅሁፍ ይጠቅሳል፡፡ አሁን መፅሃፍ ቅዱስ እያለለት ሌላ መፅሃፍ ዘንድ ምን ወሰደው ትሉ ይሆናል፡፡ መልሱ ግልፅ ነው… ሰውዮው እኮ ፍሮይድ ነው… የጥያቄ ጌታ!

የባቢሎኑን መስራች ሳርገንን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የአፈታሪክ አለም ዝነኞች ከአባቶቻቸው ጋር የማይተዋወቁ ወይም የተጣሉና በህፃንነታቸው የተወረወሩ (ወደወንዝ) ናቸው፡፡ እነሙሴ፣ ኤዲፐስ፣ ክርስቶስ፣ ሄራክልስ፣ ዜቶስ፣ ወዘተ ታሪካቸው ተመሳሳይ ነው፡፡ ሚቶሎጂው ምን እየነገረን ይሆን? የነገደ-ወይጦን ልማዶች ከጥንታዊ የግብፅ ሚቶሎጂ ጋር ማስተሳሰር ይቻል ይሆን?

አሳ-ነክ ወጎች ይቀጥላል፡፡      

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ