ሰኞ 19 ኦክቶበር 2015

አሳ ነክ ወጎች (ክፍል ፪)



አሳ ነክ ወጎች (ክፍል ፪)

ባለፈው እንዳልነው የነገደ-ወይጦ አገር አባይና ጣና ናቸው፡፡ ማንነታቸው የተቀዳው እንደውሃው ከባህሮቹ ነው፡፡ ይህም የውሃ ነዋሪው ጦጣ (Aquatic Ape Theory) የሚለውን የዝግመተ-ለውጥ መላምት እንድናስታውስ አድርጎናል፡፡ ጉዟችን በቦታና በጊዜ ላይ የሚደረግ በመሆኑ የጉዞ ማስታዎሻችንም በቦታና በጊዜ ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ አሁን በጊዜ ላይ የምናደርገውን ጉዞ እንቀጥላለን፡፡ ስለጦጣው ትንሽ ላውጋችሁ፡፡

እንደወይጦዎች ከአሳ ወገን የሆነው ጦጣ በውሃ ውስጥ ይኖር ነበር፡፡ ይህ በውሃ ውስጥና ውሃ ዳር ለዳር የሚኖር የጦጣ ዝርያ የሁላችንም ቅድመ-ቅድመ-አያት ነው፡፡ የሰው ልጅ የአሁንን ቅርፅና ተፈጥሮ ያዳበረው እንደጉማሬ በውሃ ውስጥ ይኖር ስለነበር ነው፡፡ በዚህ መላ-ምት መሰረት የሰው ልጅ ገዳይ ጦጣ አልነበረም፡፡ የሴቶችም ሚና ልጅ በማሳደግ የተወሰነ አልነበረም፡፡ ከወንዱ ጋር እኩል ውሃው ውስጥ እየተዘዋወሩ የሚበላ አሳ ነክ ነገር ይሰበስቡ ነበር፡፡ ይህ ሃሳብ ለፌሚኒስቶች ጥሩ ስንቅ ይሆናችኋል፤ ተጠቀሙበት፡፡

የሌሎች እንስሳት አንጎል እየተጨማተረ ሲሄድ የሰው ልጆች አንጎል ግን እየፋፋ ከቦርጫችን የማይተናነስ የሆነበት ምክንያት በውሃ ውስጥ ብቻ የሚገኙ ንጥረ-ነገሮችን ለመመገብ ዕድል ስላገኘን ነው፡፡ ጎረቤታችን ጉማሬ ነበር፡፡ እንዲህ አሁን ሰልጥነን ውለታቸውን ብንረሳም ከነአምባዛ ጋር ክፉ ደጉን አሳልፈናል፡፡

ሌላው የውሃ ህይወታችን ምስክር አተነፋፈሳችን ነው፡፡ ሶስት ዓይነት የአተነፋፈስ መንገዶች አሉ፡፡ በፈቃድ፣ ያለፈቃድና ሁለቱንም አተነፋፈስ የሚጠቀሙ አሉ፡፡

እንግዲህ በየብስ ላይ የሚኖሩ አጥቢዎች ሁሉ የሚተነፍሱት ከራሳቸው ቁጥጥር ውጭ በሆነ ሁኔታ ነው… ያለፈቃዳቸው፡፡ ሙሉ በሙሉ በንቃተ-ህሊና ውስጥ ሆነው በራሳቸው ፍቃድና ቁጥጥር የሚተነፍሱ እንስሳት ዶልፊንና አሳ ነባሪ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ግማሽ ያንጎላቸው ክፍል ብቻ እንቅልፍ የሚተኛው፡፡ ሙሉ ለሙሉ ከተኙማ ትንፋሹን ማን ይቆጣጠርላቸዋል?! ስለዚህ መተንፈሳቸው ስለሚያቆም ሞት ይወስዳቸዋል፡፡ ይህ እንዳይሆን በግማሽ ጎናቸው ሳይሆን በግማሽ አንጎላቸው ይተኛሉ፡፡ እግዜር ያሳያችሁ እነዚህ ምስኪኖች እንዴት ያለ እንቅልፍ እንደሚተኙ፡፡ ሶስተኛው ቡድን እንደየሁኔታው በንቃተ-ህሊና ውስጥ ሆኖ በራሱ ቁጥጥር የሚተነፍስ አልያም ደግሞ ያለቁጥጥሩ እንዲሁ የሚተነፍስ የእነእንቁራሪት ወገን ነው፡፡ ይህ ወገን በየብስና በውሃ ላይ እያፈራረቀ የሚኖርና ውሃ ውስጥ ሲገባ ትንፋሹን በመቆጣጠር የሚተነፍስ ነው፡፡

የሰው ልጅ እንደእንቁራሪት ትንፋሹን በመቆጣጠር የሚኖር ከመሰሎቹ የተለዬ ብቸኛ ፍጡር ነው፡፡ ይህን ባህርይ ከዬት አመጣው ነው ጥያቄው እንግዲህ፡፡ ይህ ባህርይ ከውሃ ዳር ኗሪነቱ የመጣ ነው ይሉናል ሊቃውንቱ፡፡

ነገደ-ወይጦ ይህን የባህር ውስጥ ህይወቱን የረሳ አይመስልም፡፡ የአሳን ውለታ ሊረሳ አልፈቀደም፡፡ የጥንቱን ከተማውን መርሳት አልፈለገም፡፡ ውሃ ዳር ኑሮውን ይገፋል፤ ውሃው ውስጥ ቀለቡን ይፈልጋል፡፡…

የውሃ ዳር ጦጣ መላ-ምት እንደሚለው ከውሃ አቅራቢያ የሚኖሩ ቀደምት ነዋሪ የዓለም ህዝቦች ልጅ የሚወልዱት ወደባህር ሄደው ነው፡፡ ሚሲዮኖች መጥፎ ልማድ ነው ብለው እስኪያስተዋቸው ድረስ እናቶች ልጆቻቸውን የሚወልዱት ወንዝ ዳር ወርደው ነው፡፡ ምጥ ሲጀምራቸውም አምቡላንስ የሚጠሩት ወደ ሆስፒታል ሳይሆን ወደ ወንዝ እንዲወስዳቸው ነው፡፡ እናቶችም በአሳ ስጋ እንጅ በገንፎ አይታረሱም ነበር፡፡ ነበር ነው እንግዲህ፡፡

ህፃናቱ ታዲያ ከመራመዳቸው በፊት ዋና ይችሉ ነበር፡፡ የሰው ልጅ ዳይቪንግ ሪፍሌክስ ፊታችን ውሃ ላይ ባረፈ ጊዜ ጉረሮአችንን እንዲዘጋ ስለሚያደርግ ህፃናቱ እንደልባቸው ይዋኙ ነበር፡፡

ይህን የህፃናቱንና የባህር ግንኙነት በቅዱስ መፅሃፍ ውስጥም እናገኘዋለን፡፡ እባካችሁ ኦሪት ዘፀዓት ላይ ግለጡ፡፡… የደንገል ሳጥን ለእርሱ ወስዳ ዝፍትና ቅጥራን ለቀለቀችው፤ ህፃኑንም አኖረችበት፤ በወንዝም ዳር ባለ በቄጤማ ውስጥ አስቀመጠችው…ይላል፡፡ የደንገሉን ሳጥን ማን ሰራላት? ወይጦ፡፡ የሆነስ ሆነና ማነው ይህ ህፃን? ሙሴ፡፡ የስሙም ትርጓሜ ከውሃ አውጥቼዋለሁ ማለት ነው፡፡ በስያሜውና በሌሎች የሙሴ ማንነት ዙሪያ ማንበብ ብትሹ የሲግመንድ ፍሮይድን “Mosses and Monotheism” ግለጡ፡፡ በፍሮይድ ገለፃ ውስጥ ሙሴ ማለት የግብፅ ቃል ነው፤ ትርጓሜውም ህፃን ማለት ነው ሲል ሌላ ፅሁፍ ይጠቅሳል፡፡ አሁን መፅሃፍ ቅዱስ እያለለት ሌላ መፅሃፍ ዘንድ ምን ወሰደው ትሉ ይሆናል፡፡ መልሱ ግልፅ ነው… ሰውዮው እኮ ፍሮይድ ነው… የጥያቄ ጌታ!

የባቢሎኑን መስራች ሳርገንን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የአፈታሪክ አለም ዝነኞች ከአባቶቻቸው ጋር የማይተዋወቁ ወይም የተጣሉና በህፃንነታቸው የተወረወሩ (ወደወንዝ) ናቸው፡፡ እነሙሴ፣ ኤዲፐስ፣ ክርስቶስ፣ ሄራክልስ፣ ዜቶስ፣ ወዘተ ታሪካቸው ተመሳሳይ ነው፡፡ ሚቶሎጂው ምን እየነገረን ይሆን? የነገደ-ወይጦን ልማዶች ከጥንታዊ የግብፅ ሚቶሎጂ ጋር ማስተሳሰር ይቻል ይሆን?

አሳ-ነክ ወጎች ይቀጥላል፡፡      

ማክሰኞ 6 ኦክቶበር 2015

ባህር ዳር (አሳ ነክ ወጎች)

ባህር ዳር (አሳ ነክ ወጎች)
(ውብሸት ታደለ)

“አሳ አበላሻለሁ
አባይ ዳር ነው ቤቴ፣
ዶሮ መረቅማ
ወዴትስ አባቴ…”


እያለ የሚያንጎራጉረው የሙዚቃ ሙሴያችን አሰፋ አባተ ነው፡፡ አሰፋ አባተ የሞተ ሰሞን ቤተሰቦቹ ድምፁን በሬዲዮ እየሰሙ ስለተረበሹ አዲስ አበባ ድረስ ሄደው የሱ ሙዚቃ እንዳይከፈት ማስደረጋቸውን አንዴ እናቴ አጫውታኛለች፡፡ የሰብለ ተፈራ የጉለሌ ማስታወቂያ በቴሌቪዥን መተላለፉ ባለመቋረጡ ተናዶ ዮሃንስ ሞላ የፃፈውን ፅሁፍ ሳነብ ይህ የአሰፋ አባተ ጉዳይ ትዝ ብሎኝ ነበር፡፡ አሁን አሰፋ አባተ ትዝ ያለኝ ግን ለሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ስለባህርዳር ህዝብ ባህል ላወጋችሁ ፈልጌ ነው፡፡ ስለባህርዳር የሚያወራ ሰው አሳን ሳይጠቅስ ማውራት ከቻለ፣ ስለርሃብ የሚያወራ ሰው ኢትዮጵያን ሳይጠቅስ ማውራት ይችላል ማለት ነው፡፡

ለሁሉም አሳና ባህርዳር ግንኙነታቸው ከተፈጥሯዊነት/አካባቢያዊነት የዘለለ አለመሆኑን ለመናገር ጠንቋይ መቀለብ አያስፈልግም፡፡ በአባይና ጣና የተከበበችው ከተማ አሳን የምታውቀው በስም ነው፡፡ ባህርዳራውያን አሳ ባህላቸው ውስጥ የለም፡፡ ፍላጎታቸው ውስጥ የለም፡፡ ከላይ የጠቀስነው የዘፈን ግጥም የሚያስረዳን የአሳ ስጋ የዶሮ መረቅን ክብር አለማግኘቱን ነው፡፡ ባህርዳሮች አሳን የሚያስታውሱት በአተነፋፈሱና በቅዱስ መፅሃፍ ውስጥ ባለው ስፍራ ነው፡፡

በሬስቶራንቶችና ሆቴሎች ውስጥ ግን አሳን ማግኘት አይቸግርም፡፡ አሳ ጥብስ፣ አሳ ዱለት፣ አሳ ክትፎ፣ አሳ ፍርፍር፣ አሳ ጉላሽ፣ ወዘተ፡፡ ብዙ ዓይነት የአሳ ምግቦች አሉ፡፡ የአማራችሁን የስጋ ምግብ ዓይነት ከፊቱ “አሳ” የሚል ቃል ጨምራችሁ ማዘዝ ነው… ይመጣላችኋል፡፡ አሳ ቅቅል ብቻ መኖሩን እጠራጠራለሁ፡፡

ባህርዳር ውስጥ አሳን በተነፃፃሪነት በብዛት የሚመገቡት ወይጦዎች ናቸው፡፡ እና ወደደሴቶቹም አካባቢ የተለመደ ሳይሆን አይቀርም፡፡

አሳ ለጭንቅላት ዕድገት ጥሩ እንደሆነ ብዙ ሰዎች ይናገራሉ፤ ሳይንሱም ይላል፡፡ የአሳ ዘይት ለህፃናት ሲያጠጡ አያለሁ፡፡ ለባህርዳራውያን ግን “የአሳ ግማቱ ከጭንቅላቱ” የዘወትር ተረታቸው ነው፡፡ ባህር ውስጥ የሚኖር ነገር አይመቻቸውማ፡፡ የባህርዳር ሰዎች ከጎንደርና ከጎጃም የተሰባሰቡ እንጅ አስቀድሞ እንደወይጦዎቹ በአባይና ጣና ዙሪያ አልነበሩም፡፡ ስለዚህ ኑሯቸው ከውሃ ዳር ከመኖራቸው ጋር ዝምድና የለውም፡፡ ባህላቸው ከባህርዳር ተፈጥሮ ጋር በተደረገ ግብግብ የመጣ አይደለም፡፡

ስለዚህ ከወይጦዎቹ ጋር ተጣሉ፡፡ በምን ተጣሉ? በአመጋገብ፡፡ ነገደ-ወይጦን ከሌላው ማህበረሰብ ሊነጥለው የቻለ ትልቅ ጉዳይ አመጋገቡ ነው፡፡ ከነገደ-ወይጦ የምግብ ሜኑ ውስጥ አሳና ጉማሬ አይጠፉም፡፡ ከጎጃሜውና ጎንደሬው ሜኑ ላይ ደግሞ ሽሮና የዶሮ መረቅ፡፡ ስለዚህ አሳና ዶሮ መግባባት ተስኗቸው ማህበረሰቡን ከሁለት ከፈሉ፡፡ አሳው ከየብስ ተገለለ፡፡ እዛው ጣናው ስር ተወሽቆ መኖር ዕጣ ፈንታው ሆነ፡፡ ነገደ-ወይጦ… ነገደ ባህር…ነገደ ጣና…

ለጎጃሜውና ጎንደሬው ንብረቱ መሬት ነው፤ ግዛቱ የብስ ነው፡፡ የወይጦ ንብረት ግን ጣና ራሱ ነው፤ ርስቱ እሱ ነው፡፡ ጎዳናው አባይ ነው፡፡ ስለዚህ ኑሮው ሁሉ በጣናና አባይ ላይ የተመሰረተ ሆኗል፡፡ ጣናና አባይ ደንገል፣ ድንጋይና ጂኒ ያመርቱለታል፡፡

በደንገሉ እንደፈርኦኖች ፊደል አይፅፍበትም፡፡

ታንኳ (ጀልባ) ይሰራበታል እንጅ፡፡ እነዚህን የአሳ ማስገሪያና የከሰል ማመላለሻ ጀልባዎች ግርሃም ሃንኮክ ተመልክቶ ቅርፃቸውን ከታቦተ-ፅዮን ጋር እንዳመሳሰለው አስታውሳለሁ፡፡ መፅሃፉ በእጃችሁ ያለ ልታርሙኝ ትችላላችሁ፡፡ ደንገሉን የእንጀራ መሶብም ይሰፉበታል፡፡ መሶቡን ገዝተው የሚጠቀሙት ጎጃሜዎችና ጎንደሬዎች ናቸው… የዶሮ መረቅ ሊበሉበት፡፡ ሌላው የደንገል ጥቅም ጎፈሬው ነው፡፡ ከደንገሉ ጫፍ ላይ ባህርዳሮች ለቤት ማስዋቢያ የሚነሰንሱት ጨፌ/ቄጤማ አለ፡፡ ወይጦ ይህንን ጎፈሬ ከደንገሉ ላይ እየላጨ ለየብሳውያን ይቸበችባል፡፡ እሱማ ሳር መሃል እየዋለ ሳር ምን ሊያደርግለት፡፡ የደንገል ጥቅም በዚህ አያልቅም፡፡ እንደጥራር ተደርጎ አጥር ይሰራበታል፡፡ ለገሳ ይሆናል፡፡ ምኑ ቅጡ!!

ደንገሉን ጨርሰን ወደ ድንጋዩ ስንገባ የድንጋይ ወፍጮ ከተፍ ይላል፡፡ የብሳውያን እህላቸውን የሚፈጩት በወይጦዎች የወፍጮ ድንጋይ ነው፡፡ ጓያቸውን እየፈጩ ያንጎራጉራሉ፡፡ የተከነች ሽሮ ሊበሉ፡፡

የሆነስ ሆነና ሶስተኛው የጣናና አባይ በረከት የሆነችው ጂኒ ምንድነች? ጂኒ ማለት የውሃ ውስጥ ሳይጣን ነች፡፡ በባህርዳራውያን ዘንድ ብዙ ነገር ይተረክላታል፡፡ ውሃው ውስጥ ቡና ስታፈላ አየናት የሚሉ አሉ፡፡ ልጆቿን ቁንዳላ ትሰራለች የሚሉ አሉ፡፡ ወዘተ፡፡ እና ይች ጂኒ በየዓመቱ ሰዎችን ከሚዋኙበት ወይም ከሚታጠቡበት እየሳበች ትወስድና ደማቸውን ትመጥጣቸዋለች ተብሎ ይታመናል፡፡ ስለዚህ አባይና ጣና ሰው በሰመጠ ቁጥር አስከሬኑን ፈልገው አውጥተው ለአቅመ-ቀብር የሚያበቁት ወይጦዎች ናቸው፡፡ ለዚህም ስራቸው ይከፈላቸዋል፡፡

ለዚህ ነው ጣናና አባይ ለነገደ-ወይጦ ደንገል፣ ድንጋይና ጂኒ ያመርቱለታል ያልኳችሁ፡፡ ጎጃሜና ጎንደሬም እንጀራውን ከወይጦ መሶብ፣ ሽሮውን ከወይጦ ድንጋይ ያገኛል፡፡ ነገር ግን ከወይጦ ጋር ባመጋገብ ጥል ናቸው፡፡ እነጎጄ የየብስ ምርት፣ እነወይጦ የባህር ምርት ይመገባሉ፡፡ የዶሮና የአሳ ጦርነት ያስነሳሉ፡፡

አሳው ወደባህሩ፡፡…

ለረጅም ጊዜ፡፡…

ከባህርዳራውያን ህይወት ተነጥሎ፡፡…

ይህንን ጉዳይ ባለቅኔው ሎሬት ጸ/ገ/መ በተለያዬ መንገድ በስራዎቹ ላይ አንፀባርቆታል፡፡ “እሳት ወይ አበባ” ላይ ‘ለበጌምድር ወይጦ ባላገር’ በሚል ማስታዎሻነት “ይድረስ ለወንድሜ ለማላውቅህ” ሲል ፅፏል፡፡ “እናት አለም ጠኑ” ቲያትር ላይ ደግሞ በገራፊው ገብረየስ አንደበት ትዕዝብቱን ያስረዳል፡፡ ተያያዢ ፅሁፎችን ቀስ እያልኩ አቃምሳችኋለሁ፡፡ “ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል” ትላለች እናቴ ስትተርት! ባንዴ ሁሉን መዘርገፍ አይቻልም፡፡ ሰፊ ነው… ውስብስብ ነው… አጨቃጫቂ ነው፡፡

ባህራውያንና የብሳውያን ባህርዳር ላይ በእንዲህ ዓይነት መልኩ ሲኖሩ የየብሳውያን ባህል ከባህሩ የራቀ ነው፡፡ አሳ የባህርዳራውያን ባህል አይደለም፡፡ ሆኖም ግን በጣና 26 የሚደርሱ የአሳ ዝርያዎች እንደሚገኙ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ነጭ አሳ፣ አምባዛ፣ ቀረሶ፣ ቤዞ፣ ወዘተ. ህዝቡ አፍ ውስጥ የማይጠፉ የአሳ ዝርያዎች ናቸው፡፡ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ “Fishery Department” ከፍቶ ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡ ከአንዱ የፊሸሪ ባለሙያ ጋር ቆይታ ማድረግ ከቻልኩ የተብራራ መረጃ ይዤላችሁ እመለሳለሁ፡፡

አሰፋ አባተ በመረዋ ድምፁ እንዲህ ሲል ይቀጥላል፡

አሳ በብርብራ የሚያሰግር ጠፍቶ
ያሳማት ያሳማት ተኝቶ

ብርብራ አሳን የሚያሰክርና ከአጥማጆቹ እጅ ላይ የሚጥል የአሳዎች አረቄ ነው፡፡ ሁሌም አጥማጆች ተጠማጆችን የሚይዟቸው በስካር ነው፡፡ አልኮል የሚያቀርብልህ ሰው ባህርህ ውስጥ ብርብራ እየጨመረ ነው፡፡

እና እላችኋለሁ…

አንዴ ጉምዞች አሳ ሲያጠምዱ ያየሁት ነገር ሁሌም አይረሳኝም፡፡ ከወንዙ ላይ ዳር እስከዳር መረብ ዘረጉ፤ ከዚያ ወደምንጩ አቅጣጫ መረቡን ይዘው መጓዝ ጀመሩ፡፡ ከዚያ መረብ ማምለጥ የሚችሉት አሳዎች አስማተኛ መሆን አለባቸው፡፡ በአሳ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈፀም አየሁ፡፡

በነገራችን ላይ አሳን በመቃጥን (መንቃሊፎ) ማጥመድ አዝናኝ ነገር ነው፡፡ የመቃጥኑ ጫፍ በቀስት ጫፍ ዓይነት የተሰራ መርፌ ነው፡፡ እዚህ መርፌ ውስጥ ዳቦ ወይም ትላትል ወይም ሌላ የአሳ ፋቮራይት የሆነ ነገር መሰካት ነው፡፡ ይህን የአሳ አጥማጆች ትዕይንት ተመልክቶ በውስጡ ህይወታችንን የሚቃኘው ገጣሚ ኑረዲን ኢሳ የኛ መንቃሊፎ የሚለውን ግጥም ያስታውሰን ዘንድ እንጠይቃለን፡፡ ኑረዲን የባህርዳር ልጅ በመሆኑ ግጥሞቹ አሳ አሳ ይሸታሉ ብዬ ላጋንን፡፡

ይህንን ፅሁፍ ልዘጋው ስል አንድ ቲዎሪ ትዝ አለኝ፡፡ ”Aquatic Ape Theory”፡፡ ይህ ቲዎሪ የዝግመተ-ለውጥ ቲዎሪ ነው፡፡

Savannah Land Theory የሰው ልጅን አመጣጥ ወደ ወደ አፍሪካ ሳቫና የሚወስድ ነው፡፡

ሌላው ከዚህ ጋር ተያያዥ የሆነ ቲዎሪ የገዳዩ ጦጣ ቲዎሪ (A Killer Ape Theory) ነው፡፡ ይህ ቲዎሪ የሰው ልጅን አመጣጥ ከገዳይነት አመሉ አጋር የሚያያይዝ ነው፡፡

አሁን ያነሳሁት Aquatic Ape Theory ከእነዚህ በተለዬ መልኩ የሰው ልጅን አመጣጥ ወደውሃ ወይም ባህር የሚወስድ ነው፡፡ ለዚህ መላ ምቱ መነሻ የሆኑት የሰው ልጅ ባህርያትን እንዘርዝር፡ በሁለት እግር መራመዱ፣ ፀጉር አልባነቱ፣ የቆዳ ስር ቅባት መያዙ፣ የትልቅ አንጎል ባለቤትነቱ፣ የቋንቋ ክህሎቱ፣ ወዘተ የባህር ላይ መሰረቱን እንደሚናገር ያስረዳል፡፡

ስለዚህ ቲዎሪ በቀጣይ ፅሁፌ በዝርዝር አወጋችኋለሁ፡፡ የነገደ-ወይጦ ህይወት፣ የአሳ ነገር እና የባህርዳራውያን ባህል አብሮን ይዘልቃል፡፡
እስከዚያው “አሳ በለው በለው” የሚለውን ዘፈን እየዘፈናችሁ ጠብቁኝ፡፡

ከአፍታ አክራሞት በኋላ እመለሳለሁ ፡)

(ይቀጥላል)