(ማማሟቂያ ማስታዎሻ)
ጣና ዳር ተቀምጫለሁ፡፡ ጣና በኢትዮጵያ ትልቁ ኃይቅ ነው፡፡ እንደገበቴ ውሃ ታይቶ የሚያልቅ ነገር የሚመስላችሁ አንባቢዎች ካላችሁ ኑ ጣናና ሰማዩ ሲሳሳሙ ተመልከቱ፡፡ ጣና ፊት ለፊት ስትቀመጡ ዕልቆ ቢስነትን ትመለከታላችሁ ፤ ደቃቅ የመሆን ስሜት ይሰማችኋል፡፡ በዚህ ሁሉ መካከል በባህርዳር ሙቀት የቀለጠውን ገላችሁን ጣና እንደትኩስ አጥሚት በትንፋሹ ያበርድላችኋል፡፡ አገር የቀየራችሁ ይመስል የደገኛን ህይወት ትለምዳላችሁ፡፡ በነገራችን ላይ የአየር ንብረት በሰዎች ባህልና ባህርይ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለመረዳት ቆለኛና ደገኛን ገበሬው የሚገልፅበትን መንገድ ማስተዋል በቂ ነው፡፡ በባህርዳር ህዝብ ባህልና ባህርይ ላይ አየር ንብረቱ ያሳደረው ተፅዕኖ ካለ በቀጣይ ፅሁፎቼ የምመለስበት ይሆናል፡፡ አሁን ወደ ጣና እንመለስ፡፡
ኃይቁ ዳር መቀመጥ የሚያመጣውን ሰላም ለማወቅ ዳር ለዳር የተኮለኮለውን ሰላም ፈላጊ መመልከት ይበቃል፡፡ ኑሮ የሰለቸው፣ ግራ የገባው፣ በሃዘን የሚብሰለሰለው፣ ችክ ይዞ በትኩስ ፍቅር የሚፈነጥዘው፣ ድሎት አሰቃይቶት ከድሎት ለማረፍ የመጣው፣ የእንግድነት ስሜቱን ከጣና ጋር በመጫወት የሚያጠፋው፣ ልጅነታቸውን በጣና ውሃ በመረጫጨትና በመዋኘት የሚያሳልፉ ህፃናት፣ ሃይቁ ዳር ተቀምጠው ጫት የሚያላምጡ ወጣቶች፣ ለሃይቁ ታዳሚዎች የተላያዩ ሸቀጦችን የሚያቀርቡ ጀብሎዎች፣ ወዘተርፈ፡፡ ኃይቁ ከባህርዳር ቤተክርስቲያናት የማይተናነስ ሚና የሚጫወት የባህርዳራውያን የሰላም ማዕከል ነው፡፡
ጨዋታ ፈልጎ ለሚዋትት ብቸኛ ኃይቁ ራሱ ያጫውተዋል፡፡
ሞገዱ ከድንጋዩ ጋር ሲማታ እንደሚታለብ ወተት አረፋ እየተፋ…
ሞገዱ ሲቀንስ ጣና ራሱ በትልቅ ብረት ድስት እንደተጣደ ውሃ ሲንተከተክ…
ከሩቅ ሲታዩ ምንነታቸውን የሚወራረዱባቸው ጀልባዎችና ታንኳዎች…
ሞገዱ ከድንጋዩ ጋር ሲጋጭ የሚፈጥረው ዘመን ተሻጋሪ (ክላሲክ) ሙዚቃ…
ጣና እንዲህ ያጫውታል፡፡
ጣና ዳር ላይ የሚታዩት ድንጋዮች ድቡልቡል እንጀራ ይመስላሉ፡፡ እነዚህ እንጀራዎች የሚርሱት በጣና ወተት ነው፡፡ የጣና ወተት በጎጃምና በጎንደር የብስ መካከል እየተናጠ የጎጃምና ጎንደርን እንጀራዎች ያርሳል፡፡ አንዳንድ ድንጋዮች ከውሃው ጋር ባደረጉት የረጅም ጊዜ ፍልሚያ ምክንያት አካላቸው እየተቦረቦረ ከእንጀራነት ይልቅ ለገበጣ መጫዎቻነት ይቀርባሉ፡፡ ይህ ነገር እንደምን ይሆናል? ውሃ እንዴት ድንጋይን ይሰባብራል? መልሱ ግልፅ ነው፡፡ እስመዓልቦ ነገር ዘይስዓኖ ለጊዜ፡፡
የድንጋይ እንጀራዎቹን ባህርዳሮች ‘የወይጦ ድንጋይ’ ይሏቸዋል፡፡ ወይጦ ማለት የባህርዳር ቀደምት ነዋሪዎች መጠሪያ ነው፡፡ ነገደ-ወይጦ ከእስራዔል ከመጡ ነገዶች አንዱ መሆኑን አለቃ ታዬ “የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክ” በሚለው መፅሃፋቸው ይገልፃሉ፡፡ ምንም እንኳን አለቃ ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝብ ከእስራኤል የመጣ ነው የሚል መሰረቱ ኃይማኖታዊ የሆነ ትረካ ቢኖራቸውም ይህ ነገድ እስከነአለቃ ድረስ ዕወቅና ያለው ነገድ እንደሆነ ያሳዬናል፡፡ ያም ሆነ ይህ ድንጋዮቹ ለምን በዚህ ነገድ ስም ተሰዬሙ ብሎ መጠዬቅ ይቻላል፡፡ ለዚህ ምክንያት ሁለት ነጥቦችን በምናልባት ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ አንደኛው የነገደ-ወይጦ ማህበረሰብ ከጣና ኃይቅ ጋር ባለው የቆዬ ቁርኝት ምክንያት የጣናን ሁለንተና ከዚህ ማህበረሰብ ጋር የማያያዝ ልማድ አለ፡፡ ሁለተኛው ነጥብ ይህ ማህበረሰብ (ቢያንስ በአሁኑ ጊዜ) እነዚህን ድንጋዮች ለእህል ወፍጮነት አዘጋጅቶ በመሸጥ ይተዳደራል፡፡ ስለነገደ-ወይጦ ማህበረሰብ በቀጣይ ፅሁፎቼ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ይዤ እመለሳለሁ፡፡ አሁን ወደጣና ልመለስ…
ጣና እጅግ ሰፊ ኃይቅ ነው፡፡ ባህርዳር ላይ ተቀምጦ ጣናን የሚመለከት እንግዳ በጣና ስፋት ሊገረም ይችላል፡፡ ከሚያዬው የጣና ክፍል ውጭ ኃይቁ ያለ አይመስለውም ይሆናል፡፡ እውነቱ ግን ባህርዳር በጣና ጭራ ላይ የተቋጠረች ከተማ መሆኗ ነው፡፡ ባህርዳር የከበበችው የጣና ክፍል ከሃይቁ ጠቅላላ ስፋት ጋር ሲነፃፀር የኃይቁ ጭራ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የጣና ¾ ኛ ከፍል የሚገኘው በጎንደር ክፍለሃገር ነው፡፡ ባህርዳር በጣና ዙሪያ የተመሰረተች ከተማ ብትሆንም ስፋቷ ከጣና የተወለደች ግልገል ያስመስላታል፡፡ የከተማዋ ሁለንተና ጣና ጣና ይሸታል፡፡ የትኛውም የባህርዳር አካባቢ ላይ ተቀምጣችሁ ከጣና ልትርቁ አትችሉም፤ ቢያንስ ነፋሱ ይደርሳችኋል፡፡ ከኃይቁ ዳር ለዳር ዙሪያውን የተዘረጋው የእግረኛ መንገድ ጣናን እየተዟዟሩ ለመጎብኘትና በንፋሱ እየቀዘቀዙ ወክ ለማድረግ እጅግ ምቹ ነው፡፡
ለማንኛውም አሁን ጣና ዳር ነው የተቀመጥኩት፡፡ በኮከል መናፈሻ ውስጥ፡፡ ይህች ትንሽዬ መናፈሻ በጣና ለመዝናናት አመች ከሆኑ ቦታዎች አንዷ ስትሆን ወደጣና ሾጠጥ ብላ ከገባች የየብስ ቁራጭ ላይ የተመሰረተች ውብ ቦታ ናት፡፡ ዝርዝር ብር ይዛችሁ ልትዝናኑባት የምትችል ትንሽዬ መናፈሻ፡፡
ከዚች መናፈሻ ላይ ሆኜ ከጣና ጋር ስጫወት አዕምሮዬ ፊት ለፊቴ ወደሚገኙትና አሁን ወደማይታዩኝ ደሴቶች ወሰደኝ፡፡ እነዚያ ደሴቶች ላይ ታሪክ ራሱ እንደዘንዶ ተጠቅልሎ ተኝቷል፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ከክርስቶስ ልደት በፊትና በኋላ እነዚህ ደሴቶች ዘንድ ይገኛል፡፡ ከጥንቱ የታቦተ-ፅዮን አፈታሪክ ተነስተን በእነ አምደፅዮን የመካከለኛው ዘመን ታሪክ ሾልከን ወደዘመናዊቷ ኢትዮጵያ እናዘግማለን፡፡ ወደእነዚህ ደሴቶች መጓዝ በጊዜ ማሽን ላይ ወደኋላ እንደመጓዝ ይመስለኛል፡፡ ለሁሉም ወደእነዚህ ደሴቶች ሄጄ ታሪክና እውነትን እስካወጋችሁ ድረስ ጓጉቻለሁ፡፡ ጉዞው በኃይቅ ላይ ብቻ ሳይሆን በጊዜ ላይም ነው፡፡ መልካም ጊዜ!
